መቅድም
GSAM 3.1ብዙ ጠቃሚ መጻሕፍት አስቀድመው በሕዝቡ እጅ ይገኛሉ። በእነዚህ ላይ ሌላ መጽሐፍ ለመጨመር ያለኝ ምክንያት፣ በእነዚህ ገጾች ስለ አድቬንቲስቶች፣ በተለይም የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶችን በሚመለከት፣ ከዚህ በፊት በዚህ መልክ ለሕዝቡ ያልቀረቡ ብዙ ነገሮችን መግለጼ ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ በኋለኞቹ ዓመታት ይህን ዓላማ የተቀበሉ፣ የተጠቀሱትንም ነገሮች በዓይናቸው ያላዩ ብዙዎች፣ በሥራው ቀድመው የነበሩት እነዚህን እውነታዎችና ተሞክሮዎች እንዲተርኩላቸው አጥብቀው ጠይቀዋል። በ1843 እና 1844 የአድቬንት እንቅስቃሴን በቅርብ ስለማውቅ፣ ከጃንዋሪ 2, 1849 ጀምሮም መጀመሪያ እንደ አድቬንቲስት፣ ከ1852 ጀምሮ ደግሞ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ሆኜ ትምህርቱን ስላወጅሁ፣ “ያየሁትንና የሰማሁትን መናገር” ደስ ያሰኘኛል።
GSAM 3.2ከ1831 እስከ 1844 ድረስ በዓለም ወደ ሁሉም የሠለጠኑ አገሮች ስለተስፋፋው የአድቬንት እንቅስቃሴ ዘገባ አቅርቤአለሁ።
GSAM 3.3ከ1845 ጀምሮ የክርስቶስ መምጣት መቅረቡን ያወጁ፣ እስከ አሁንም የሚያውጁ ሌሎች የአድቬንቲስቶች ወገኖች ነበሩ። የእነዚህን ሁሉ ታሪክ ከመከታተል ይልቅ፣ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶችን አመጣጥና እድገት በተወሰነ ዝርዝር ለመግለጽ ዓላማ አድርጌአለሁ። በተለይም በእግዚአብሔር አመራር፣ ከድህነትና ከትንሽ ጅማሬ ተነሥተው እንዲያድጉ የረዱአቸውን መንገዶች ለማሳየት ፈልጌአለሁ። ቁጥራቸው ወደ አንድ መቶ ሺህ ብቻ ቢሆንም፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎቻቸው እንኳ፣ “ከሚሠሩበት ብርታትና ቅንዓት የተነሣ፣ ቁጥራቸው ሁለት ሚሊዮን እንደሆነ ሰው ሊገምት ይችላል” ብለዋል።
GSAM 3.4የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ታሪክን በጥቂቱ የሚያውቁ እንኳ፣ ከ1845 ጀምሮ ወይዘሮ ኢ. ጂ. ዋይት በተናጋሪነትም በጸሐፊነትም ከእንቅስቃሴው ጋር ጉልህ ግንኙነት እንደነበራቸው ያውቃሉ። ከሥራቸው ጋርም ልዩ መገለጦች ወይም ስጦታዎች እንደነበሩ ያውቃሉ። ይህ ስጦታ ሲሠራ ወደ ሃምሳ ጊዜ ተገኝቼ ለማየት ዕድል አግኝቻለሁ። በእነዚህ ገጾች፣ ወይዘሮ ዋይት የተናገሩአቸውና እጅግ በትክክል የተፈጸሙ ወደ ሃያ ስድስት የሚሆኑ ግልጽ ትንቢቶችን አመልክቻለሁ።
GSAM 4.1እኔ ካየሁት በተጨማሪ፣ ሌሎች በዓይናቸው ያዩ ሰዎች ስለ ተሞክሮዎቻቸው የሰጡትን ምስክርነትም አቅርቤአለሁ። ሐቀኛ አንባቢ፣ በእነዚህ አጋጣሚዎች ፈጽሞ ተገኝተው የማያውቁ ሰዎች ከሚሰጡት እንዲሁ የተወረወረ ንግግር ይልቅ፣ እንደዚህ ላሉ እውነታዎች የበለጠ ክብደት ሊሰጥ ይገባል።
GSAM 4.2በእግዚአብሔር በረከት፣ እነዚህን ገጾች ማንበብ በብዙ ልቦች ውስጥ የክርስቶስን ሥራ ለማስፋፋት መንገድ እንዲሆን ተስፋ በማድረግ፣ ይህን መጽሐፍ ለአንባቢዎች አስረክባለሁ። ሁሉም ሲያነቡ፣ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች የተናገረውን፣ “ሁሉን ፈትኑ፤ መልካሙን አጥብቃችሁ ያዙ።” የሚለውን ቃል በልባቸው እንደሚያስቀምጡ እተማመናለሁ።